let's talk
በኢትዮጵያ በግሉ ዘርፍ የመጀመሪያው የሕይወት እና የጤና ኢንሹራንስ የአክስዮን ሽያጭ 81 በመቶ መጠናቀቁ ተነገረ
መጋቢት 22/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በመቋቋም ላይ የሚገኘው በኢትዮጵያ በግሉ ዘርፍ የመጀመሪያው ሙሉ በሙሉ የሕይወት እና የጤና ኢንሹራንስ የአክሲዮን ሽያጭ 81 በመቶ መጠናቀቁን የፋሚሊ ጤና ሕይወት ኢንሹራንስ አስታውቋል።

"በግሉ ዘርፍ ለረጅም ጊዜ ሙሉ በሙሉ የጤና ኢንሹራንስ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም አልነበረም" ያሉት የፋሚሊ ኢንሹራንስ አደራጅ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ይራይፍሬ ስለሽ፤ ይህን ችግር ለመቅረፍ ፋሚሊ የሕይወትና ጤና ኢንሹራንስ ባለፋት አራት ወራት ለምስረታ የሚያበቃውን ካፒታል ማሰባሰቡን እና ቅድመ-ዝግጅት መጨረሱን ተናግረዋል፡፡

ፋሚሊ የሕይወትና ጤና ኢንሹራንስ አዲስ አበባን ጨምሮ ከሰባት የኢትዮጵያ ክልሎች የተውጣጡ ከ45 በላይ ሆስፒታሎች ስፔሻሊቲ ሕክምና ማዕከላትና ዲያግኖስቲክ ማዕከላት በጋራ በመሆን የመሰረቱት መሆኑንም ለአሐዱ ገልጸዋል።

እነዚህም ተቋማት ለኢንሹራንሱ ደንበኞች ጥራት ያለው ሕክምና ስለሚሰጡበትና ጤና ሚኒስቴር በዘረጋቸው ወሳኝ ኢኒሼቲቮች ላይ በትብብር ስለሚሰሩበት ማዕቀፍ ሰፊ ውይይት መደረጉን አብራርተዋል።

ምክትል ሰብሳቢው አክለውም፤ እየተቋቋመ የሚገኘው ፋሚሊ የጤና ሕይወት ኢንሹራንስ የአክስዮን ሽያጭ 81 በመቶ ወይም 320 ሚሊዮን ብር ተከፍሎ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ፋሚሊ የጤና ሕይወት ኢንሹራንስ ከአስፓየር ማይክሮ ፋይናንስ ጋር አብሮ ለመስራት የስትራቴጂክ አጋርነት ስምምነት ተፈራርሟል።

የአስፓየር ማይክሮ ፋይናንስ ዋና ሰብሳቢ የሆኑት ዶክተር ካሳሁን ይመር ማይክሮ ፋይናንሱ በመቋቋም ላይ መሆኑን ገልጸው፤ ፋሚሊ ኢንሹራንስ አገልግሎት ሲጀምር የሚገኙ ገንዘቦች በትክክል ሥራ ላይ እንዲውል የሚያደርግ የፋይናንስ ተቋም አስፈላጊ በመሆኑ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ተናግረዋል።

የአስፓየር ማይክሮ ፋይናንስ የአክስዮን ሽያጩን 25 በመቶ ማጠናቀቁን የገለጹት ዋና ሰብሳቢው፤ ባለአክሲዮኖች ከ50 በታች ስለሆኑ በሚቀጥሉት ሁለት ወይም ሶስት ወራት ውስጥ ወደ ሥራ ይገባል ብለዋል።

በአበረ ስሜነህ